ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ልጆች ቤት ውስጥ ከማስቀመጥ ይልቅ ወደ ትምህርት ቤት መላክ በተለይ ከተሞች ላይ እየተለመደ ቢመጣም፣ የራሱ የሆኑ ውስንነቶች አሉበት፡፡ የአካቶ ትምህርት እየተተገበረ ቢሆንም፣ በቂ የልዩ ፍላጎት መምህራን ማግኘትና ለእነሱ የሚመጥን ሥርዓተ ትምህርት አለመኖር ከችግሮቹ ይጠቀሳሉ፡፡

‎የጉዳታቸው መጠን ከፍተኛ የሆኑ ልጆችን በቤት ውስጥ አሊያም እንደ ችግራቸው መጠንና ዓይነት በሚያስተናግዱ የግል ማዕከላት እንክብካቤ እንዲያገኙ የሚያደርጉ ወላጆች አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለልጆቻቸው ሲሉ ቤት የሚውሉና ሥራ ባለመሥራታቸው ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግር የሚጋለጡም አይጠፉም፡፡ በተለይም ዓይነ ሥውር ልጅ ያላቸው ወላጆች ለልጆቻቸው የሚሆን ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት በማጣታቸው ከፍተኛ ፈተና ይደቀንባቸዋል።

‎ዓይነ ሥውሯ ሕፃን አትናሲያ ገለታ የሰባት ዓመት ታዳጊ ብትሆንም፣ በትምህርቷ የአፀደ ሕፃናት (ኬጂ) ሦሰት ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ የቻለችው ግን በመንግሥት በኩል ለዓይነ ሥውራን ሕፃናት የተዘጋጀ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት በመኖሩ ሳይሆን፣ ዓይነ ሥውራን ልጆች ያሏቸው ወላጆች ባቋቋሙት ነፃ ትምህርት ቤት በመማሯ ነው፡፡

‎ወላጅ እናቷ ወ/ሮ ገነት ብሩ እንደተናገሩት፣ ዓይነ ሥውራን ሕፃናትን ተቀብሎ የሚያሰተምር መዋለ ሕፃናት ወይም ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ባለመኖሩና፣ የልጆቹ ዕድሜ አሥርና ከዚያ በላይ ሲሆን የሚሄዱት ሻሸመኔና ሰበታ ወደሚገኙ ዓይነ ሥውራን ትምህርት ቤቶች በመሆኑ ዓይነ ሥውር ልጅ ያላቸው ወላጆች ሲቸገሩ ቆይተዋል፡፡

‎ችግሩን ለመቅረፍና ዓይነ ሥውራን ሕፃናትም አንደ እኩዮቻቸው የትምህርት ዕድል አንዲያገኙ ለማስቻልም፣ በወላጆች አማካይነት ‹‹ቪዥን ማየት የተሳናቸው›› ትምህርት ቤትን ከአራት ዓመት በፊት በማቋቋም ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡