በአለምአቀፍ ደረጃም ሆነ በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፏ መምጣታቸው ተጠቁሟል።

ይህ የተባለው በዛሬው እለት በኢትዮጵያ ለ8ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም አቀፍ  የሕሙማን ደህንነት ቀንን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው መድረክ ላይ ነው።የጤና ሚኒስቴር ከአለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር አለም አቀፍ የሕሙማንን ደህንነት ቀንን አስመልክቶ መድረኩን ያዘጋጀ ሲሆን እለቱም‹‹ ደህንነቱ የተጠበቀ ክብካቤ ለጤናማ ህይወት በሚል መሪ ቃል ›› በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል በተለያዩ መርሃ-ግብሮች እየተከበረ ይገኛል።

የሪዞልቭ ቱ ሴቭ ላይቭ በኢትዮጵያ ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ግርማ አሰፋ ለብስራት ሬድዮ እንደተናገሩት በአለም አቀፍ ደረጃ አራት ህይወታቸው ከሚያልፉ ሰዎች ሶስቱ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የተነሳ ህይወታቸውን ያጣሉ። ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያም ጎልቶ እንደሚታይ ተናግረው በቀን 600 የሚሆኑ ሰዎች በዚህ በሽታ ህይወታቸው ያልፋል ነው ያሉት።ከጉዳዮ ጋር በተያያዘ የህክምና አገልግሎት ማዕቀፉ ተደራሽነትን ለማሳደግ ብዙ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ዶክተር ግርማ መረጃዎችን ጠቅሰው እንደተናገሩት በኢትዮጵያ በደማቸው ውስጥ የደም ግፊት አለባቸው ተብለው የሚጠበቁ አዋቂዎች ከ11 እስከ 12 ሚሊዮን ይገመታሉ።እንደ የደም ግፊት፣ የስኳር፣ የልብ፣ የደም ቧምባ በሽታ እና የካንሰር ህመም ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች መካከል በዋነኛነት ተጠቃሽ ሲሆኑ የሚፈለገውን የጤና ግብ ለማሳካት የታካሚ ደህንነት እና እንክብካቤ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑ ተመላክቷል።

በመሆኑም በዘንድሮው የህሙማን ደህንነት ቀን ለጉዳዮ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ውጤታማ ስራ ለመስራት ያግዛል ተብሏል።