በጂቡቲ ወደብ ከስምንት ወራት በላይ ቆመው የሚገኙና ግምታቸው ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሆኑ ከ4 500 በላይ የሚሆኑ የከባድ ጭነትና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካዎች አስመጪዎች፣ ተሽከርካሪዎቹን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የገንዘብ ሚኒስቴርንና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርን ይሁንታን ባለማግኘታቸው፣ ለከፍተኛ ኪሳራ እየተዳረጉ መሆኑን ጠቁመው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መፍትሔ እንዲሰጧቸው ጥያቄ ማቅረባቸው ታወቀ፡፡

‎ተሽከርካሪዎቹ በጂቡቲ የቆሙበት ምክንያት፣ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረት በመጀመሯ ምክንያት ከመሰከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በቤንዚንና በናፍጣ የሚሠሩ የጭነትና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር በቁጥር ገ/ኢ/1/9/88/2018 ባስተላለፈው መመሪያው ምክንያት መሆኑን ሪፖርተር የተመለከታቸው ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

‎የአገሪቱ ከፍተኛ ግብር ከፋይና የከባድ ጭነት፣ የሕዝብ ማመላለሻና የተለያዩ ተሽከርካሪዎችን እንደሚያስመጡ፣ በተለያዩ ሰነዶ ላይ ድርጅታቸውና ስማቸው የተጠቀሱ ከመቶ በላይ የሚሆኑ አስመጪ ነጋዴዎች እንደሚያስረዱት፣ ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በተሰጣቸው ተሽከርካሪዎችን የማስገቢያ ፈቃድ መሠረት ‹‹በነዳጅና ናፍጣ›› የሚሠሩ ተሽከርካዎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ከመከልከሉ በፊት፣ ግዥ ከሚፈጽሙባቸው ተሽከርካሪዎችን አምራች አገሮች ግዥ ፈጽመው ያስጫኑ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ 

‎ገንዘብ ሚኒስቴርም ተሽከርካሪዎች እንዳይገቡ በጻፈው ደብዳቤ (መመሪያ) በግዥ ሒደት ላይ ያሉና ግዥያቸው ተጠናቆ የተጫኑ ተሽከርካሪዎች እስከ ስድስት ወራት ድረስ ክልከላው ሳይመለከታቸው እንዲገቡ መፍቀዱን ሰነዶቹ ያስረዳሉ፡፡

‎አስመጪዎቹ ገንዘብ ሚኒስቴር መመሪያ ከማስተላለፉ በፊት በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ የማስገቢያ ፈቃድ አግኝተው ኤልሲ (LC) በመክፈት፣ ከአምራች አገሮች ጋር የግዥ ውል ፈጽመው ተሽከርካሪዎቹ እንዲጫኑ በማዘዝ፣ አንዳንዶቹ ቀረጥና ታክስ ጭምር በመክፈል፣ ተሽከርካሪዎቹን ወደ አገር ውስጥ የማስገባት ሒደት አስጀምረው እንደነበር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት የአቤቱታ ደብዳቤ ላይ ገልጸዋል።

‎ተሽከርካሪዎቹን ከወደብ ማንሳት ያልተቻለው በአንድ በኩል የአፈጻጸምና የማጣራት ሒደት ጊዜ በመውሰዱ ተያያዥ በሆኑ አስተዳደራዊ ክፍተቶች ምክንያት በተፈጠረው ችግር ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‎አስመጪዎቹ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት አቤቱታና መፍትሔ መፈለጊያ ደብዳቤ እንዳስረዱት፣ በሕጋዊ አሠራር ሒደት ኤልሲ (LC) በመክፈትና የባንክ የክፍያ ሥርዓት ለውጭ አቅራቢዎችና አምራቾች የተላለፈ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ የተከፈለባቸው ከ4,500 በላይ ከባድ የጭነትና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች በጂቡቲ ወደብ ቆመው በቀን ከ90,000 ዶላር ባላይ ደሜሬጅ እየተከፈለባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በየቀኑ ከሚከፈለው የውጭ ምንዛሪ በተጨማሪ፣ ተሽከርካሪዎቹ በጂቡቲ ባለው ከፍተኛ ሙቀትና ጨው ከፍተኛ የቴክኒክና አካላዊ ጉዳት እይደረሰባቸው መሆኑን፣ የዴሜሬጅ ባለመከፈሉ የጂቡቲ መንግሥት ተሽከርካሪዎቹን በጨረታ የመሸጥ አደጋ እንደተረጋገጠባቸው፣ ተሽከርካሪዎቹን ለመግዛት ከተለያዩ ባንኮች ለወሰዱት የውጭ ምንዛሪ በዋስትና ያስያዙት ንብረት (ኮላተራል) በሐራጅ የመሸጥ አደጋ እየደረሰባቸው መሆኑን፣ በብሔራዊ ባንክ በForeign Exchange Delinquent List ውስጥ የመመዝገብ አደጋ እያጋጠማቸው መሆኑን ጠቁመው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መፍትሔ እንዲሰጧቸው ተማጽነዋል፡፡ መንግሥት ተሽከርካሪዎቹ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ቢያደርግ፣ ከታክስና ቀረጥ (ባለፉት ወራቶች) ከ1.8 ቢሊዮን ብር በላይ ያገኝ የነበረውን ገቢ ማጣቱን በጉምሩክ ኮሚሽን በተጣራ መረጃ መረጋገጡን አክለዋል፡፡

‎ከተሽከርካሪዎቹ ጋር በተያያዘ ጉምሩክ ኮሚሽንም በጂቡቲና በአገር ውስጥ ስለቆሙት ተሽከርካሪዎች በሚመለከት በቁጥር 4/2840/18 ግንቦት 11 ቀን 2018 ዓ.ም. ለገንዘብ ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ፣ በቤኒዚንና ናፍጣ የሚሠሩ የጭነትና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ ከመስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ እንዳይገቡ መከልከሉን፣ ቀደም ብሎ በሒደት ላይ የነበሩትንና በተፈቀደው ሰድስት ወራት ውስጥ ጂቡቲ ደርሰው የቆሙ ተሽከርካዎችን በሚመለከት መፍትሔ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡