አሜሪካዊቷ የሀገረ ሰብ ሙዚቃ አቀንቃኝ: የዜማ ደራሲት፣ ተዋናዪትና በጎ አድራጊ ዶሊ ፓርተን ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው ነሐሴ 19 ቀን 2018 ዓ.ም. ነው፡፡ እንደ ቢቢሲ ዘገባ፣ ዶሊ ከሀብታም ቤተሰብ የተገኘች አልነበረችም፡፡ እ.ኤ.አ. በ1946 ቴነሲ ግዛት ውሰጥ የተወለደችው ዶሊ፣ ያደገችው መብራትና ውኃ በሌለው ቤት ውስጥ አሷን ጨምሮ ከ12 አህትና ወንዶሞቿ ጋር ነበር።

‎ሆኖም ዶሊ ለድህነት አልተበገረችም፡፡ ሕይወቷን የቀየረው አጋጣሚ በ11 ዓመቷ ቢጀምርም፣ የዘፈን ግጥም መጻፍ የጀመረችው በስድስት ዓመቷ እንደነበር በእሷ ዙሪያ የተጻፉ የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ለስኬቷ ደግሞ የሙዚቃ ደራሲ የነበረው አጎቷ ዊልያም ኤርል ኦውንስ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡

‎ከ60 ዓመታት በላይ በቆየው የጥበብ ጉዞዋ 49 የስቱዮ አልበሞችን የለቀቀችው አቀንቃኟ፣ ከ3,000 በላይ ዘፈኖችንም ጽፋለች፡፡ ከዶሊ ፓርተን ተወዳጅ ዘፈኖች መካከል እ.ኤ.አ. በ1974 የጻፈችውና የዘፈነችው ‹‹ጀሊን›› አንዱ ሲሆን፣ ለግጥሟ መነሻውም ባለቤቷ ካርል ዲን አንዲት ሴት ሲያሽኮረምም በማየቷ እንደነበር ዘ ኮንቨርሴሽን ዘግቧል። በዚሁ ዓመት የዘፈነችውና በኋላም በ1992 ዓ.ም. ለቦዲጋርድ ፊልም ማጀቢያ በዊትኒ ሂውሰተን ተዘፍኖ የዓለም መነጋገሪያ የሆነውን ‹‹አይ ዊል ኦሎይስ ላቭ ዩ›› የተሰኘው ሙዚቃዋም ተጠቃሽ ነው፡፡

‎የግራሚ 11 ሽልማቶችን የወሰደችው ዶሊ፣ በሙዚቃዋ ብቻ ሳይሆን በልግስናዋም ትታወቃለች፡፡ ከሙዚቃ ሥራዋ ጎን ለጎን በበጎ አድራጎት ሥራዋ በተለይም በልጆች ትምህርትና ንባብ ላይ ትኩረት በመስጠትም፣ ኢማጅኔሽን ቤተ መጻሕፍት አቋቁማለች፡፡ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅትም የክትባት ምርምር እንዲፋጠን አንድ ሚሊዮን ዶላር ለግሳለች፡፡

‎በተወለደች በ80 ዓመቷ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለየችው ታዋቂዋ የሀገረ ሰብ ሙዚቃ ኮከብ ዶሊ ፓርተን ክብር፣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ ለአንድ ሳምንት ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡