ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት መስከረም 29 ቀን 2018 ዓ.ም. በይፋ ካስጀመረች ወዲህ፣ ባለፉት ስምንት ወራት ወደ ሰባት የአፍሪካ አገሮች ከላከቻቸው ምርቶች ከ14.4 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቷን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያገኘነው የንግድ ልውውጥ አፈጻጸም ሰነድ እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያ ከጥቅምት ወር 2018 ዓ.ም. መግቢያ ጀምሮ በአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና (AFCFTA) ስምምነት ማዕቀፍ ውስጥ ንግድ እያካሄደች ነው፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ7.1 ሚሊዮን ኪሎ ግራም በላይ ምርቶች ወደ ሰባት የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በመላክ፣ ከ14 ሚሊዮን 408 ሺሕ 467 ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቷን መረጃው ያሳያል።
በዚህ የንግድ ሥርዓት ኢትዮጵያ ወደ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ጋና፣ አልጄሪያ ምርቶችን ስትልክ ከኬንያ፣ ከግብፅና ከታንዛኒያ ደግሞ የተለያዩ ምርቶችን ስታስገባ ከ5.7 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማድረጓ ተገልጿል።
የቅባት እህሎችና ውጤቶች፣ በቆሎ፣ የኬሚካልና የንፅህና መጠበቂያ ምርቶች ከኢትዮጵያ ወደ ሌሎች አገሮች የተላኩ የምርት ዓይነቶች ናቸው፡፡ ከውጭ የገቡት ደግሞ እርሾ፣ ሰው ሠራሽ ፀጉርና የቴሌቪዥን ክፍሎች ናቸው᎓᎓ ንግዱ በይፋ ከመጀመሩ በፊት በነበሩት ዘጠኝ ወራት ኢትዮጵያ ምርቶቿን በከፍተኛ መጠን የላከችባቸው አገሮች ጋና፣ ኬንያ፣ ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ ሲሆኑ፣ ንግዱ ከተጀመረ በኋላ አልጄሪያ፣ ታንዛኒያና ሩዋንዳ ተጨምረው ሰባት ደርሰዋል ተብሏል። የመዳረሻ አገሮች ቁጥር መጨመር ነፃ ንግድ ቀጣናው በፈጠረው የታሪፍ ቅናሽ ዕድልን ከመጠቀም የመነጨ እንደሆነ ሰነዱ ያስረዳል።
ሰነዱ እንደሚያሳየው ከሆነ 37 ድርጅቶች በወጪ ንግድ፣ 76 ድርጅቶች ደግሞ በገቢ ንግድ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከሌሎች አባል አገሮች ባካሄደችው ንግድ እስካሁን 240 የስሪት አገር ምንጭ ሰርተፊኬት እንደተሰጣቸው ተገልጿል።
የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት የአፍሪካ አገሮችን የእርስ በርስ ንግድ ለማሳደግ፣ ነፃ የሰዎችና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ፣ የጋራ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ገበያ ለመፍጠር ዓላማ ተደርጎ የተመሠረተ ነው፡፡ የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣናን ከፈረሙት 54 የአፍሪካ አገሮች ውስጥ እ.ኤ.አ. በየካቲት 2026 በወጣ የሴክሬታሪያቱ መረጃ መሠረት 50 አገሮች ስምምነቱን በሕግ አውጪ አካላቸው አፅድቀዋል።