የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ለዓመታት በግንባታ ላይ ለነበረው የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የዘርፍ ሦስት (ካታጎሪ 3) ጨዋታዎችን እንዲያስተናግድ ጊዜያዊ ፈቃድ ሰጥቷል። በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) መስከረም 19 ቀን 2019 ዓ.ም. በሜዳውና በደጋፊው ፊት ከሴኔጋል አቻው ጋር የሚያደርገው የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በዚሁ ስታዲየም እንደሚከናወን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይፋ አድርጓል፡፡

‎ካፍ ከያዛቸው አራት ዓይነት የስታዲየም ደረጃዎች ውስጥ ዘርፍ ሦስት የዋናውን ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያዎች እንዲሁም የክለቦች የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ እስከ ምድብ ድልድል ድረስ ያሉ ጨዋታዎችን የሚያካትት ነው፡፡

‎ከአምስት ዓመታት በፊት በወጣው የካፍ ዕገዳ ምክንያት ዋሊያዎቹ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጨዋታዎቻቸውን ከአገራቸው ውጪ በሚገኙ ስታዲየሞች እንዲጫወቱ መገደዳቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ይህም በብሔራዊ ቡድኑ የሜዳ ተጠቃሚነት ላይ ተፅዕኖ ከማሳደሩ ባሻገር ፌዴሬሽኑን ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ ዳርጎ ቆይቷል።

‎የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብርሃም ገብረ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ካፍ የስታዲየም ደረጃዎችን በሚመለከት አራት ዓይነት መሥፈርቶችን (ስታንዳርዶችን) ይከተላል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ዘርፍ አንድና ዘርፍ ሁለት የሚባሉት የታዳጊ ወጣቶች፣ ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች ቡድኖች፣ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎች) እንዲሁም የክለቦች ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች የሚካሄዱባቸው መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ አቶ አብርሃም አክለውም ባለፈው ዓመትና ከዚያም በፊት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ሲደረጉ የነበሩ ጨዋታዎች የዚሁ ዘርፍ አንድና ዘርፍ ሁለት መሥፈርት ማሳያ እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

‎በቅርቡ በባህር ዳር ስታዲየም የተደረገውን የግንባታ ሒደት የገመገመው የካፍ ባለሙያ ቡድን፣ የዳኞች መቀየሪያ ክፍሎችና የክብር እንግዶች (ቪአይፒ) ክፍሎች፣ የሜዳው ሳር ሁኔታም ለዘርፍ ሦስት ጨዋታዎች መስፈርቱን ማሟላታቸውን አረጋግጧል። ሆኖም ስታዲየሙን የሚያስተዳድረው አካል የመጨረሻውን ዘርፍ አራት (ካታጎሪ 4) መስፈርት ለማሟላት ያልተጠናቀቁ ግንባታዎችን አሁን ባገኘው ጊዜያዊ ፈቃድ ሳይዘናጋ በፍጥነት ማስተካከል እንዳለበትና ይህ የማይሆን ከሆነ ካፍ ፈቃዱን መልሶ ሊያነሳ እንደሚችል አሳስቧል።